ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የአንካራው ስምምነት እንዳይፈጸም የሚጥሩ አካላትን ተፅዕኖ ለመከላከል መከሩ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የደኅንነት ተቋማት የአንካራው ስምምነት ተፈጻሚ እንዳይሆን እንቅፋት የሚፈጥሩ አካላትን ተፅዕኖ ለመከላከል ምክክር አደረጉ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የተቋሙ ስትራቴጂክ አመራሮች ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት የሶማሊያ ናሽናል ኢንተለጀንስ ኤንድ ሴኪዩሪቲ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አብዱላሂ ሞሐመድ ዓሊ ጋር በወቅታዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
የአንካራውን ስምምነት ተግባራዊ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ከሁለቱ ሀገራት አቻ ተቋማት የሚጠበቁ የትብብርና የአጋርነት መስኮች ላይ ውይይት መደረጉን አገልግሎቱ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የላከው መረጃ አመላክቷል፡፡
በውይይቱም የኢትዮጵያና ሶማሊያ የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማት ስምምነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት የሚፈጥሩ አካላትን ለመከላከል የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት የጋራ መግባባት መድረሳቸው እና በተለይም በመረጃ ልውውጥ አቅጣጫ መቀመጡ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነት የሚያደፈርሱ አጋጣሚዎች ተፈጥረው እንደነበር ያስታወሰው መረጃው÷ የሁለቱ ሀገራት ዕድገት የተሳሰረ መሆኑ እንዲሁም በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የዘለቀው አብሮነት ግንዛቤ ውስጥ እንደሚገባ በመድረኩ መነሳቱ ተጠቅሷል፡፡
አሸባሪው አልሸባብ አሁንም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሥጋት ምንጭ መሆኑን የኢትዮጵያና የሶማሊያ የደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በምምከር መድረኩ አንስተዋል፡፡
የነበሩትን የዳበሩ ልምዶች በመቀመርና አዳዲስ የጸረ-ሽብር ትግል አጋርነትና ትብብር መስኮችን በማጠናከር ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል መስማማታቸውም ነው የተገለጸው፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሊያ የጋራ ስጋቶችን በትብብርና በምክክር በመፍታት ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማስፈንና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ተባብረው እንደሚሠሩም በውይይቱ ተነስቷል፡፡