ናሳ ለፀሐይ ቅርብ በሆነ ርቀት መንኮራኩር ለማሳለፍ ጥረት እያደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ጣቢያ (ናሳ) ፓርከር ሶላር ፕሮብ ለፀሐይ ቅርብ በሆነ ርቀት መንኮራኩሩን ለማሳለፍ ጥረት እያደረገ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ከምድር በ6 ነጥብ 2 ሚሊየን ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው መንኮራኩር ፀሐይን በቅርብ ርቀት ለማሳለፍ እየጣረ ሲሆን፤ ሙከራው እስከዛሬ ከተደረጉት ሙከራዎች የአሁኑ ለፀሐይ የቀረበ መሆኑ ተነግሯል።
መንኮራኩሩ በፀሐይ ጎን በሚያልፍበት ወቅት ከምድር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አይኖረውም ያሉት የናሳ ሳይንስ ሃላፊ ኒኮላ ፎክስ (ዶ/ር)፤ ተልእኮው በሰላም መጠናቀቁን ለማወቅ እስከ ፈረንጆቹ ገና ዋዜማ ድረስ መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
ተልእኮው ከፀሐይ ርቆ የሚገኘውን እና በሚሊየን ዲግሪ በሚቆጠር ሞቃታማ የሆነውን ኮሮና የተሰኘ ክፍል ወሳኝ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም ስለፀሐይ ንፋስ እንዲሁም በፀሐይ ወደምድር በሚለቀቁ ቅንጣቶች ላይ ጥናት የማድረግ ዓላማም እንዳለው ተመላክቷል።
ለዚህ ተልዕኮ የተዘጋጀው የጠፈር መንኮራኩር በሰአት 430 ሺህ ሜትር የሚጓዝ ሲሆን ከፍተኛ ሙቀትን እና ጨረሮችን መቋቋም እንዲችል ተደርጎ መሰራቱንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የፀሐይ እንቅስቃሴን እና ጠፈርን መረዳት በምድር ላይ ለዕለት ተዕለት ህይወታችን በጣም አስፈላጊ ነው ያሉት ኒኮላ ፎክስ (ዶ/ር)፤ የተልዕኮውን የተሳካ ምላሽ ሁሉም በጉጉት እየጠበቀው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡