የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር ትራንስፖርት እንቅስቃሴን የፀጥታ ሁኔታ ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር ትራንስፖርት እንቅስቃሴን የፀጥታ ሁኔታ ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል።
የውይይቱ ዓላማ የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር መሥመርን አልፎ አልፎ በመሠረተ ልማት ላይ ከሚፈፀም ወንጀል ነፃ ለማድረግና ከሌሎች የወንጀል ስጋቶች ማፅዳት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር እና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን÷ በፀጥታው ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በጥናት ለመለየት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
አመራሮቹ ባለድርሻ አካላትን በጉዳዩ ላይ በማወያየትና የአካባቢው ኅብረተሰብን ግንዛቤ በማሳደግ በባቡር ትራንስፖርቱ መስመር ላይ እየተፈፀሙ ያሉትን ውስን የፀጥታ ችግሮች ለመቅረፍ በቁጠኝነት ለመስራት መስማማታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡