የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኞች ቁጥር 4 ነጥብ 9 ሚሊየን ደረሰ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ 600 ሺህ አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሠራሁ ነው ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገልጿል፡፡
ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ጀምሮ 167 ሺህ 952 አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን እና አጠቃላይ የደንበኞቹ ቁጥርም 4 ሚሊየን 936 ሺህ 912 መድረሱን ተቋሙ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
በሀገር አቀፍ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ከ1998 ዓ.ም በፊት የኃይል ተጠቃሚ የሆኑ የገጠር ከተሞች 667 እንደነበሩ አስታውሶ፤ ይህ አሃዝ አሁን ላይ 8 ሺህ 245 መድረሱን አረጋግጧል፡፡
ከ25 ሚኒ ግሪድ ግንባታ አንጻርም ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ ርቀው የሚገኙ አካባቢዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በተሠራው ሥራ ሦስቱ ተጠናቅቀው 74 ሺህ 222 ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ያለው፡፡
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 74 በመቶ የደረሰ ሲሆን÷ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 126 ሺህ 788 አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብሏል፡፡
በዮሐንስ ደርበው