ሀገር አቋራጭ መንገዶች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተደረገባቸው መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር አቋራጭ መንገዶች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተደረገባቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ትላልቅ መንገዶች ላይ አስተማማኝ ጥበቃ እየተደረገ ነው፡፡
ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ባሕርዳር፣ ሰመራ፣ ጅቡቲ፣ ሞያሌ፣ ነቀምቴ፣ ደምቢዶሎ፣ ጋምቤላ፣ ጅግጅጋ እና ሌሎች ከተሞች የሚያቀኑ መንገደኞችን ደህንነት ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት ከአዲስ አበባ-ባሕርዳር፣ ከአዲስ አበባ-ሰመራ -ጅቡቲ እና ሌሎች መንገዶች ላይ ጸረ ሰላም ሃይሎች አልፎ አልፎ ችግር ይፈጥሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይም ፌዴራል ፖሊስ ከመከላከያ ሰራዊትና ከክልል ጸጥታ ሃይሎች ጋር በቅንጅት በሰራው ሥራ ዋና ዋና ሀገር አቋራጭ መንገዶች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተደረገባቸው ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በተለይም በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪ በመቀበላቸው አብዛኛዎቹ መንገዶች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሳቸውን አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ጸረ ሰላም ሃይሎችና የመንገድ ዘራፊዎች አልፎ አልፎ ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ጠቁመው÷ ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከአዲስ አበባ-ባሕር ዳር የሚሰሩ የሕዝብ ማመላለሻና የከባድ መኪና ሾፌሮች በበኩላቸው ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት÷ በመንገዱ ከዚህ በፊት በተለይም በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ታጣቂዎች መንገደኞችን ከማገት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ጥቃት ያደርሱ ነበር፡፡
አሁን ላይ ግን የአዲስ አበባ-ባሕር ዳር መንገድ ላይ ዘራፊዎች አልፎ አልፎ ከሚፈጥሩት ችግር በስተቀር ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያስተናገደ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ-ሰመራ-ጅቡቲ መንገድ የሚሰሩ አሽከርካሪዎች÷ ሀገር አቋራጭ መንገዱ አስተማማኝ ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑን ጠቁመው፤ መስመሩ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሽከርካሪዎቹ በሀገር አቋራጭ መንገዶች ላይ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለማስወገድ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅትና በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ