Fana: At a Speed of Life!

ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ከ310 ሺህ ቶን በላይ ሲሚንቶ ለገበያ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ተመርቆ ሥራ የጀመረው ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ እስከ አሁን ከ310 ሺህ ቶን በላይ ሲሚንቶ ለገበያ አቀረበ፡፡

ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ሲገባ በቀን 15 ሺህ ቶን (150 ሺህ ኩንታል) ሲሚንቶ የማምረት አቅም እንዳለውም ለፋና ዲጂታል አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከፊል ወደ ሥራ የገባው ፋብሪካው በቀን እስከ 10 ሺህ ቶን ሲሚንቶ ለገበያ እያቀረበ መሆኑን እና ሥራ ከጀመረ አንስቶ ከ310 ሺህ ቶን በላይ ሲሚንቶ ለገበያ ማቅረብ መቻሉን ነው የገለጸው፡፡

ፋብሪካው ገበያውን መቀላቀሉን ተከትሎም ዋጋ መረጋጋት መፈጠሩ እና የአቅርቦት እጥረት አለመኖሩ ተመላክቷል፡፡

በአጠቃላይ ፋብሪካው ለበርካታ ወገኖች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩም ነው የተገለጸው፡፡

ፋብሪካው መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም ተመርቆ ሥራ ሲጀምር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)÷ ይህ ሜጋ ፕሮጀክት የመንግሥታችን በፍጥነት፣ በግዝፈት እና በንፅህና የመገንባት ጽኑ አቋም ማሳያ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ-ልማቶችን በፍጥነት እና በብቃት አጠናቅቆ ዝግጁ የማድረግ ተምሳሌት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ ተመሳሳይ ፋብሪካዎች ተደምረው የሚያመርቱትን 50 ከመቶ የሚያመርት እንደሆነም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.