ዶናልድ ትራምፕ የሞት ቅጣትን አጠናክረው እንደሚተገብሩ አስታወቁ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአስተዳደር ዘመናቸው የሞት ቅጣትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።
የ78 ዓመቱ ዶናልድ ትራምፕ ይህን ያሉት ባለፈው ሳምንት ጆ ባይደን 37 የሞት ፍርድ ለተበየነባቸው ወንጀለኞች ፍርዱን ወደ ዕድሜ ልክ እስራት መቀየራቸውን ተከትሎ ነው።
ትራምፕ በቀጣዩ ወር ስራ ሲጀምሩ የፍትሕ ዲፓርትመንቱ የሞት ቅጣትን ተግባራዊነት አጠናክሮ እንዲቀጥል መመሪያ እንደሚያስተላልፉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት÷ወንጀለኞችን በሞት መቅጣትን አጠናክረን የምንተገብረው አሜሪካዊያንን “ከደፋሪዎች፣ ገዳዮችና ጭራቆች” ለመጠበቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ትራምፕ ጆ ባይደን ለሞት ፍርደኞች ወደ ዕድሜ ልክ እስራት ያደረጉትን ማሻሻያ አስመልክተው ሲናገሩ÷ “የእያንዳንዳቸውን ወንጀለኞች ድርጊት ብትሰሙ የፕሬዚዳንቱን ድርጊት ማመን ትቸገራላችሁ፤ ግራ ያጋባል!” ብለዋል፡፡
በዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ የፕሬዚዳንትነት ዘመን 13 ሰዎች የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ሲሆን÷ አሁንም ህጻናትን በሚደፍሩ፣ አሜሪካዊያን ዜጎችንና የሕግ አስፈጻሚ አካላትን በገደሉ ፍልሰተኞች እንዲሁም በዕፅ እና ሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ላይ የሞት ቅጣትን አጠናክረን ተግባራዊ እናደርጋለን ማለታቸውን ስካይ ኒውስ ዘግቧል።
ጆ ባይደን በአሜሪካ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ከነበሩ 40 ወንጀለኞች ውስጥ የ37 ፍርደኞችን ወደ ዕድሜ ልክ እስራት መቀነሳቸው ይታወሳል፡፡