Fana: At a Speed of Life!

ከታገዱ የሩሲያ ንብረቶች የተገኘ 1 ቢሊየን ዶላር ለዩክሬን በብድር ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከታገዱ የሩሲያ ንብረቶች የተገኘ 1 ቢሊየን ዶላር ትርፍ በብድር መልክ መቀበሏን ዩክሬን አስታወቀች፡፡

ሞስኮ በንብረቶቿ ላይ የሚወሰድ ማንኛውም ርምጃ “ስርቆት” እንደሆነ እንዲህ ያለው ርምጃም ዓለም አቀፋዊ ሕግን የሚጻረር ፣ የምዕራባውያንን ገንዘብ ምንዛሪ ብሎም የዓለም የፋይናንስ ሥርዓትና ኢኮኖሚን የሚያዳክም መሆኑን መግለጿ ይታወሳል፡፡

የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ሽሚጋል በታገዱ የሩሲያ ንብረቶች ከተገኘ 20 ቢሊየን ዶላር የአሜሪካ ብድር ውስጥ የመጀመሪያው 1 ቢሊየን ዶላር ለሀገራቸው መሰጠቱን ይፋ አድርገዋል፡፡

ይህ የሆነው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ዲፓርትመንት ለዩክሬን ለመስጠት ያቀደንውን 20 ቢሊየን ዶላር ለዓለም ባንክ ገቢ ካደረገ ከሁለት ሣምንታት በኋላ ነው ተብሏል፡፡

እንዲሁም የአውሮፓ ሕብረት ለድጋፉ ተጨማሪ 20 ቢሊየን ዶላር እንዲሁም ብሪታኒያ፣ ጃፓን እና ካናዳ ደግሞ 10 ቢሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡

በአጠቃላይ ዩክሬን ከ40 ዓመታት በላይ በሆነ ጊዜ የምትመልሰው 50 ቢሊየን ዶላር በብድር መልክ ለመስጠት በተገባው ቃል መሠረት ወደ ተግባር መገባቱ ተገልጿል፡፡

ለዩክሬን ብድሩ መሰጠት የጀመረው ከማይንቀሳቀሱ የሩሲያ ንብረቶች በተገኘ ትርፍ ነው፡፡

ሩሲያና ዩክሬን በፈረንጆቹ 2022 የካቲት ወር ላይ ጦርነት ሲጀምሩ ምዕራባውያን ሀገራት የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ንብረት የሆነውን 300 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማገሀዳቸው ይታወሳል፡፡

የአውሮፓ ሕብረትም በአባል ሀገራቱ እንዳይንቀሳቀሱ ከታገዱ የሩሲያ ንብረቶች የሚገኘውን ትርፍ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ ለማስታጠቅ ሊያውል መሆኑን ማሳወቁ ይታወቃል፡፡

የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ “ሁሉም የሩሲያ ንብረቶች ተወርሰው ዩክሬንን ለመገንባት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ እንጠብቃለን” ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ዩክሬን ከጃፓን እና ብሪታኒያ 1 ቢሊየን ዶላር በዓለም ባንክ ፕሮግራም ማግኘቷን ገልጸዋል፡፡

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው፥ ሞስኮ በንብረቷ ላይ ”በስርቆት ” ተሳትፈዋል ባለቻቸው አካላት ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንደምትወስድ ማስጠንቀቃቸውን አርቲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.