መንገደኞችን ያሳፈረ አውሮፕላን በካዛኪስታን ተከሰከሰ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 62 መንገደኞችንና አምስት ሰራተኞችን የጫነ አውሮፕላን በካዛኪስታን አክታው ከተማ አቅራቢያ መከስከሱ ተሰምቷል፡፡
ከአደጋው እስካሁን 27 ሰዎች በሕይወት የተረፉ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ፥ የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራዊት እሳቱን ማጥፋቱንና በህይወት የተረፉ ሦስት ህፃናትን ጨምሮ በአቅራቢያው በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጿል።
የሩሲያ የዜና ወኪሎች ኢምብሬር 190 የተባለው የበረራ ቁጥር ጄ2-8243 አውሮፕላን በሩሲያ ቼቺኒያ ከባኩ ወደ ግሮዝኒ ሲበር የነበረ ቢሆንም በግሮዝኒ ጭጋግ ምክንያት ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲዞር መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
የአዘርባጃን አየር መንገድ እስካሁን በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር እንደሌለም ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
የካዛክስታን ባለስልጣናት ቴክኒካል ችግርን ጨምሮ ስለተፈጠረው ነገር ምርመራ ማድረግ መጀመራቸውን የሩስያ ኢንተርፋክስ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።