የገጠር ኮሪደር ልማት አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻሉ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገጠር ኮሪደር ልማት አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚና ዘመናዊ ስልተ-ምርት እንዲከተል ማድረጉን የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ በገጠር የሚኖረው ሕዝብ የሀገሪቱ መሰረታዊ የኢኮኖሚ አቅም መሆኑን የገለጹት አቶ ሽመልስ÷ በአመራረትና አኗኗር ዘይቤ ችግሮች ስለመኖራቸው አንስተዋል።
የኮሪደር ልማቱ አርሶ አደሩ ባህሉንና ወጉን ጠብቆ አካባቢውን ንጹህ፣ ጓሮውን በዶሮ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም በማርና ወተት ምርት የተትረፈረፈ በማድረግ ቀላል የአኗኗር ስልት እንዲከተል ያደርጋል ብለዋል፡፡
የገጠር ኮሪደር ልማት የተሻለ መሰረተ ልማት በመዘርጋት በገጠርና በከተማ መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት የሚያጠብ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተጨማሪም አርሶ አደሮች ደረጃውን የጠበቀ ቤት በመስራት ከባንክ ገንዘብ መበደርና ሃብት መፍጠር የሚችሉበትን እድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት “በቁልቁሉማ” መርሐ-ግብር የገጠር ቤቶችን የአሰራር ደረጃ እንዲወጣላቸው በማድረግ የቤት ካርታ ባለቤት የሚያደርጋቸውን ህጎች እያወጣ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
የገጠር ኮሪደር ልማት አርሶ አደሩ በግቢው ውስጥ ትራክተርና መኪና የሚያቆምበትን ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ የመፍጠር ሂደት መሆኑን ገልጸው÷ በተበጣጠሰ መንገድ ሲከናወኑ የነበሩ ስራዎችን የማስተሳሰር ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በማስፋት የገጠር ኮሪደር ልማት በሰራባቸው አካባቢዎች ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ መሆኑን ጠቁመው የልማት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።