Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት የክልሉን የ2013 ዓመት በጀትን ጨምሮ የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶችን አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሶማሌ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዛሬው እለት አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በመደበኛ ጉባዔውም የክልሉን የ2013 ዓመት በጀትን ጨምሮ የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶችን ተመልክቶ አጽድቋል።

በዚህም የክልሉ ምክር ቤት 22 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ሆኖ የቀረበለትን የ2013 የክልሉ መንግስት በጀትን ተመልክቶ አጽድቋል።

ከዓመታዊ በጀቱ 17 ነጥብ 2 ቢሊየን ብሩ ከፌደራል መንግስት በሚገኝ ድጎማ የሚሸፈን ሲሆን፥  ቀሪው 5 ነጥብ 1 ቢልየን ብር ደግሞ በክልሉ የውስጥ ገቢ የሚሸፈን መሆኑም ተመልክቷል።

ምክር ቤቱ በጉባኤው የ2012 የክልሉን መንግስት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት በመመልከት ያፀደቀ ሲሆን፥ የክልሉን የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የ2012 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርትን ተመልክቷል።

በተመሳሳይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዓመታዊ ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ አቅርቧል።

በጉባኤው የ8 ዳኞች ሹመት ለምክር ቤቱ ያቀረበ ሲሆን፥ ምክር ቤቱም የቀረበውን የዳኞች ሹመት በመመልከት በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

በተጨማሪም የመንግስት ስራተኞች አደረጃጀት ማሻሻያ አዋጅን፣ የገቢ ግብር አስተዳደር አዋጅን እና ለስራ ምዘና እና ውጤት አሰጣጥ( JEG) የተጠየቀ ተጨማሪ በጀትን ምክር ቤቱ ተመልክቶ ማጽደቁን ኢቢሲ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.