Fana: At a Speed of Life!

9 ነጥብ 8 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠር መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ሶስት ዓመታት 9 ነጥብ 8 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች እውቀትን መሰረት ያደረገ ቋሚ የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

ሚኒስትሯ ባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ለማሳለጥ ብሎም የሀገሪቷን ልማት ለማፋጠን የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

ብቁ የሰው ሀይልን በማፍራት ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ፖሊሲዎች፣ አዋጅ እና የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ተግባራዊ ማድረጉን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩም በእነዚህ ዓመታት በክህሎት የዳበረ አምራች ዜጋን የመፍጠር እና የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

እንደ ሀገር ዜጎችን ከክህሎት አኳያ ማብቃት እና የስራ እድል መፍጠር ብቻ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነት የማያረጋግጥ በመሆኑ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነትን ሰላማዊ ማድረግ ላይም መሰራቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪ ብቁ እና ሙያ ያለው ዜጋን ለማፍራት የዘርፉን አሰራርና የተቋማትን የስልጠና አሰጣጥ ስርዓቶችን ማዘመን የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

ለላፉት ሶስት ዓመታትም አጫጭር የክህሎት ልማት ተግባራት ተጠናክረው የቀጠሉበት መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት 9 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች አጫጭር ስልጠናዎች በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስርዓት እንዲያልፉ መደረጉን አብራርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.