Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ሔክታር መሬት በማረስ ምርታማነትን ማሳደግ ተቻለ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የሚታረሰውን መሬት 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ሔክታር በማድረስ ዓመታዊ የምርት መጠኑን ማሳደግ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የሰላምና ደኅንነት ስራዎችን ከልማት ተግባራት ጋር አስተሳስሮ የመምራት ተግባርም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አቶ አረጋ አረጋግጠዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በምርታማነትና እድገት ተጨባጭ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው÷ በተለያዩ ዘርፎች የተገኘውን ውጤት ተከትሎም ጥቅል ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ውጤት መምጣቱን አንስተዋል።

በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና የቴክኖሎጂ ብዝኃ የኢኮኖሚ ዘርፎች ስብራትን በመጠገን የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና እውን የሚያደርጉ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

በአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት፣ የትራክተርና ኮምባይነርን የእርሻ የሜካናይዜሽን ተደራሽነቶች ላይ የተሰሩ ስራዎችም የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ያስቻሉ ናቸው ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ቀደም ሲል ለሰብል ልማት 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ሔክታር ይታረስ እንደነበር አስታውሰው፥ ይህ አሃዝ ከለውጡ በኋላ ወደ 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ሔክታር መድረሱንና ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን አንስተዋል፡፡

በ2015/16 የግብርና ምርት ዘመን ወቅት 4 ነጥብ 8 ሚሊየን የአፈር ማዳበሪያ መሰራጨቱን ጠቁመው፥ በተያዘው የምርት ዘመንም ከ7 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ተሰራጭቷል ነው ያሉት፡፡

በክልሉ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በጤፍ፣ በቆሎና ስንዴ የሰብል አይነቶች የተሰሩ የግብርና ልማት ስራዎችም አይነተኛ ለውጥ አምጥተዋል ብለዋል።

በከተማና በገጠር በሌማት ትሩፋትና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የተከናወኑ ተግባራትም የዜጎችን የአመጋገብ ሥርዓት በማሻሻል ተጠቃሚነትን እያሳደጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በሰሊጥ፣ በማዕሾ፣ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች እንዲሁም ሌሎችም የግብርና ልማቶች ስኬታማ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች የተሳኩ እንዲሆኑ በትብብር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የልማት አጋር እንዲሆኑ ተደጋጋሚ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.