የፋና ላምሮት የምዕራፍ 18 ውድድር ቅዳሜ ፍጻሜውን ያገኛል
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ላለፉት ሶስት ወራት በአስደናቂ ተወዳዳሪዎች ሲካሄድ የቆየው የፋና ላምሮት የምዕራፍ 18 ውድድር የፊታችን ቅዳሜ ፍጻሜውን ያገኛል።
ለፍጻሜው የደረሱት ማዕረግ ሀይሉ፣ እየሩሳሌም አሰፋ፣ ግሩም ነብዩ እና እዮቤል ፀጋዬ በሶስት ዙር የመረጧቸውን ሙዚቃዎች በዕለቱ ከዛየን ባንድ ጋር ያቀርባሉ።
በደማቅ ሥነ-ሥርዓት በሚካሄደው በዚህ የፍጻሜ ውድድር ላይ አንድ አንጋፋ ሙዚቀኛ በተጋባዥ እንግድነት ይታደማል።
ለውድድሩ ፋና ቴሌቭዥን የአንድ ሚሊየን ብር ሽልማት ያዘጋጀ ሲሆን÷1ኛ ደረጃ ለሚይዝ ተወዳደሪ 400 ሺህ ብር ፣ ለ2ኛ ደረጃ 300 ሺህ ብር ፣ ለ3ኛ ደረጃ 200 ሺህ ብር እንዲሁም 4ኛ ደረጃን ለሚያገኝ ተወዳዳሪ የ100 ሺህ ብር ሽልማት ይበረከታል፡፡
አራቱ የምዕራፍ 18 የፍጻሜ ተወዳዳሪዎች ለ5ኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በቀጥታ ማለፋቸውን ባለፈው ሳምንት አረጋግጠዋል።
የቅዳሜው የፍጻሜ ውድድር በሁለቱም የፋና ቴሌቭዥን ቻናሎች፣በፋና ኤፍኤም 98.1 እና በክልል ኤፍኤሞች እንዲሁም በፋና የፌስቡክ እና የቴሌግራም ገጾች በቀጥታ ይተላለፋል።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ቅዳሜ ከ6 ሰዓት ጀምሮ በቀጥታ ሥርጭት የሚካሄደውን የፍጻሜ ውድድር በመከታተልና በ8222 አጭር የጽሑፍ መልዕክት በዕለቱ የሚገለጸውን የተወዳዳሪዎች ኮድ በመላክ እየተዝናናችሁ እንድትደግፉ ይጋብዛል፡፡
በለምለም ዮሐንስ