አልማ በጤና፣ በትምህርትና በስራ ዕድል ፈጠራ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታህሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አማራ ልማት ማህበር (አልማ) ባለፉት አምስት አመታት በጤና፣ በትምህርትና በስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ስኬታማ ተግባራትን አከናውኗል ሲሉ የማህበሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ ገለጹ፡፡
በማዕከላዊ ደቡብ ወሎና ሰሜን ጎጃም ዞኖች ተግባራዊ የሚደረገው ሁለተኛ ዓመት የእናቶችና ህፃናት ጤና ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል፡፡
አቶ መላኩ ፈንታ በዚህ ወቅት ÷አልማ በጤና ፣በትምህርትና በስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም አልማ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በ55 ቢሊየን ብር ወጪ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እንደሚያከናውን ተናግረዋል፡፡
በፕሮጀክቶቹ ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያግዙ 20 ሺህ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ እንደሚከናወን ተጠቁሟል።
በጤናው ዘርፍ 373 የጤና ኬላዎች ተገንብተው የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚከናወንም ተገልጿል፡፡
የክልሉን ህዝብ በዘላቂነት ተጠቃሚ ለማድረግ ከተለያዩ አለምአቀፍ ድርጅቶችጋር በጋራ እየሰራ ስለመሆኑም ተነስቷል፡፡
የልማት ማህበሩ በክልሉ የእናቶችና የህጻናትን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የሚያስችለውን የ575 ሺህ ዶላር የድጋፍ ስምምነት ከተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ጋር መደረጉም ተጠቁሟል፡፡
በምናለ አየነው