የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በድምቀት ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታህሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ሜታ ወረዳ የሚከበረው የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በድምቀት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማደረጉን የፀጥታ ጥምር ኃይል አስታወቀ፡፡
የመከላከያ ሠራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ፣ የድሬዳዋ ፖሊስ እና የሐረሪ ፖሊስ በጋራ በመቀናጀት በቂ ዝግጅት በማድረግ ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልፀዋል።
የፀጥታ ጥምር ኃይሉ በኦሮሚያ ክልል የምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች እንዲሁም ከምስራቅ ሸዋ ዞን ጀምሮ በአካባቢው አሰሳ እና በዋና ዋና መንገዶች ፍተሻ በማድረግ ከአስተዳደር አካላት፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመተባበር ታዳሚዎች በዓሉን በሰላም አክብረው እንዲመለሱ አስተማማኝ የፀጥታ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።
የክብረ በዓሉ ታዳሚዎችን የሚያጓጉዙ አሽከርካሪዎች የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ሕግን በማክበር በኃላፊነት ማሽከርከር እንዳለባቸውም የጥምር ፀጥታ ኃይሉ ማሳሰቡን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአካባቢው ሕብረተሰብ የተለመደ የእንግዳ ተቀባይነት ባህሉን በማሳየት ለእንግዶች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግና ለፀጥታ ስጋት የሚሆኑ ሁኔታዎችን ሲመለከት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (EFPApp) በመጠቀም ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 በመደወል ጥቆማ በመስጠት ወይም መረጃውን በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት በአካል በማድረስ የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡