የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 60 በመቶ ማድረስ ተችሏል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታህሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ወደ 60 በመቶ ማሳደግ መቻሉን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
ሚኒስትሩ መላኩ አለበል÷ ባለፉት የለውጥ አመታት የአምራች ኢንዱስትሪውን ተግዳሮቶች ለመፍታት እና ተወዳዳሪ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች ለኤክስፖርት ብቻ ሳይሆን ለሀገር ውስጥ ገበያ ማምረት እንዲችሉ ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ተወዳዳሪነታቸው እንዲያድግ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አንስተዋል።
በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ላይ ማሻሻያ በመደረጉ፤ ከለውጡ በፊት ወደ 46 በመቶ ወርዶ የነበረው የማምረት አቅም አሁን ላይ ወደ 60 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ነው የገለጹት።
ከለውጡ በፊት 30 በመቶ የነበረው የአምራች ኢንዱስትሪው የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ አሁን ላይ ወደ 40 በመቶ ማድረስ መቻሉንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአምራች ኢንዱስትሪው የውጭ ባለሀብቶች ፍሰትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው ወደ ማምረት የሚገቡ የከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ቁጥርም እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በአመት በዘርፉ ለዜጎች የሚፈጠረው የስራ እድል የመፍጠር አቅምም 156 ሺህ በላይ መድረሱን አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል።