በቦክሲንግ ዴይ ጨዋታዎች የአሸናፊነት ክብረ ወሰን ያላቸው ክለቦች
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንቼስተር ዩናይትድ 21 የገና በዓል ዋዜማ ወይም ቦክሲንግ ዴይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ የክበረ ወሰን ባለቤት ነው፡፡
የግሬት ማንቼስተር ከተማው ክለብ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ከተደረጉ 32 ጨዋታዎች 21ዱን ማሸነፍ የቻለ ሲሆን÷ 76 ጎሎችን በተጋጣሚው መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል፡
የአሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ቡድን በቦርንማውዝ ከደረሰበት ሽንፈት በማገገም በዛሬው የቦክሲንግ ዴይ ጨዋታ ዎልቭስን በማሸነፍ ለደጋፊዎቹ የገና በዓል ስጦታ እንደሚያበረክት እና የቦክሲንግ ዴይ ድል ሪከርዱን ከፍ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
ሊቨርፑል እና አርሰናል 17 ጊዜ የገና በዓል ዋዜማ ጨዋታዎችን በማሸነፍ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ክለቦች ናቸው፡፡
ቼልሲ፣ቶተንሃም ሆትስፐር፣ኤቨርተን፣ማንቼስተር ሲቲ፣ብላክበርን ሮቨርስ፣ዌስትሃም ዩናይትድ እና አስቶንቪላ ደግሞ በቅደም ተከተል እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በተቃራኒው በገና በዓል ዋዜማ ጨዋታ አሳዛኝ ሪከርድ ያለው ክለብ ኒውካስል ዩናይትድ ሲሆን÷ ካለፉት 32 የቦክሲንግ ዴይ ጨዋታዎች በ15 ሲሸነፍ 45 ጎሎች ተቆጥረውበታል፡፡
እንግሊዛዊው አጥቂ ሀሪ ኬን በቦክሲንግ ዴይ ጨዋታዎች 10 ጎሎችን በማስቆጠር የክበረ ወሰን ባለቤት ሲሆን÷ የቀድሞው የሊቨርፑል አጥቂ ሮቢን ፎውለር በዘጠኝ እና የኮቭንትሪ ሲቲው አጥቂ ሮቢ ኪን በስምንት ጎል ሁለተኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
የቀድሞው የኒውካስል ዩናይትድ አጥቂ አላን ሽረር በተመሳሳይ ስምንት ጎሎች እና የቀድሞው የአርሰናል አጥቂ ቲየር ሄንሪ በሰባት ጎሎች ተከታዩን ደረጃ የያዙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡