የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ ሂደት ተቀራርቦ የመስራትና የመነጋገር ባህልን ያመጣ ነው – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ ሂደት ተቀራርቦ የመስራትና በሃሳብ የበላይነት የመነጋገር ባህልን ያመጣ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የፖለቲካ ባህል ለመገንባት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የለውጥ ሙከራዎች እንደነበሩ አስታውሰው የለውጡ መከራዎች ዋነኛ መነሻም የፖለቲካ ስብራት መሆኑን ገልጸዋል።
የ2010 ዓ.ም የለውጥ መነሻም የፖለቲካ ስብራቶች መሆናቸውንና በተለይም ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት አለመገንባት፣ የነጻና ገለልተኛ ተቋማት ግንባታ ችግር፣ አሰባሳቢ የሆነ ገዥ ትርክት አለመፍጠር፣ ደካማ የፖለቲካ ባህልና ሌሎችንም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ማናቸውንም ችግሮች በውይይት ከመፍታት ይልቅ የግጭትና ጦርነት አዙሪቶች እስካሁንም ለዘለቁ ችግሮች ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል።
የለውጡ መንግስት እነዚህን ስር የሰደዱ የፖለቲካ ስብራቶች ለመጠገን የተለያዩ የመፍትሄ ርምጃዎችን በመውሰድ የሚታዩና የሚጨበጡ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ ሂደት ተቀራርቦ የመስራትና በሃሳብ የበላይነት የመነጋገር ባህልን ያመጣ መሆኑን እና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስብራቶች የሚጠግኑ ገዥና አሰባሳቢ ትርክቶችን መፍጠር ያስቻሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።
በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ ማንኛውንም ሀሳብ ወደ ጠረጴዛ እንዲያመጡ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን አንስተው መንግስትም በሆደ ሰፊነት ወደ ውይይት እንዲመጡ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በዋናነት በታኝ የነበረውን ዋልታ ረገጥና የነጠላ ትርክት በመተው አሰባሳቢና ገዥ ትርክት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።