በኢትዮጵያ ክትባት ለማምረት የአዋጭነት ጥናት ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ክትባት ለማምረት የአዋጭነት ጥናት ለማድረግ የጤና ሚኒስቴር እና ቴክኢንቬሽን ላይፍኬር ኩባንያ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የመግባቢያ ሰነዱ መፈረም በኢትዮጵያ ክትባት ለማምረት የሚረዳ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የአፍሪካ ሀገራት በራሳቸው አቅም ክትባት ለማምረት መነሻ እንደሆነ አስታውሰው፤ በሀገር ውስጥ ክትባት ማምረት የህብረተሰብ ጤናን ለማረጋገጥ እና ለወረርሽኝ ዝግጁነት ቅድሚያ የሚሰጠው ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የክትባት ጥራት ደረጃዎችን በሟሟላት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለሌሎች ሀገራት ክትባት ለማቅረብ ብቁ እንደሆነች መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።
ክትባት ለማምረት የግንባታ እና የምርት ሂደቶችን ለመጀመር ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፤ የአዋጭነት ጥናቱን ለማድረግ ለተመረጠው የህንዱ ቴክኢንቬሽን ላይፍኬር ኩባንያ አስፈላጊው ትብብር እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
የቴክኢንቬሽን ላይፍኬር ኩባንያ ዳይሬክተር እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይድ ኤስ. አህመድ ኢትዮጵያ በቅርቡ የክትባት አምራች ሀገር እንደምትሆን እምነታቸውን ገልጸው፤ ድርጅታቸው ጥናቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ እንደሚያስርክብ ተናግረዋል፡፡