Fana: At a Speed of Life!

ለቢሾፍቱ እድገት የአየር ኃይሉ አስተዋፅኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለቢሾፍቱ ከተማ ለውጥና እድገት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አስተዋፅኦ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

ሌተናል ጄኔራል ይልማ ለከተማዋ ኮሪደር ልማት ተቋሙ ከባለሀብቶችና የልማት አጋር ግለሰቦች ጋር በመተባበር ያስገነባቸውን የልማት ፕሮጀክቶችን ከከተማው ለተውጣጡ የባለሃብቶች ቡድን አስጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ከባለሀብቶች ጋር ውይይት ያደረጉት ሌ/ጄ ይልማ፤ የቢሾፍቱ ከተማና አየር ኃይል የረዥም ዘመናት ቁርኝት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ አየር ኃይሉ ለከተማው ዕድገት አሻራ ማስቀመጡን ተናግረዋል።

ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ስማርት ሲቲ ለማድረግ በተጀመረው የኮርደር ልማት ላይ አየር ኃይሉ ንቁ ተሳታፊ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በከተማዋ ለተመዘገበው የእስካሁኑ ስኬት ባለሀብቱ እና የልማት አጋር የሆኑ ግለሰቦች ድርሻ እንዳላቸው ገልጸው፤ ይህ አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመላክተዋል።

ከከተማ አስተዳድሩ ጋር በልማት፣ በፀጥታና በሌሎችም ተያይዥ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብሮ እንደሚሰራና የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ማረጋገጣቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል።

የከተማዋ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀው፤ አየር ኃይሉን ጨምሮ ለልማቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.