Fana: At a Speed of Life!

የቅዱስ ገብርዔል ዓመታዊ የንግስ በዓል በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉ ተገለፀ

 

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ታሕሣሥ 19 የሚከበረውን የቁልቢ እና የሐዋሳ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉ ተገለፀ፡፡

የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው ብለዋል ፡፡

የመኝታ፣ የምግብ፣ የመጠጥ እና የመዝናኛ አገልግሎት የሚሰጡ እንዲሁም በሌሎች የንግድ ተቋማት ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ከንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች ጋር ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም እንግዶች በማደያዎች አካባቢ የነዳጅ ወረፋ እንዳያጋጥማቸው ብቻቸውን የሚስተናገዱባቸው ሁለት ማደያዎች መዘጋጀታቸውን፣ ወንጀል ሲያጋጥም ተጠርጣሪው ተይዞ ውሳኔ የሚሰጥበት ጊዜያዊ ችሎት መቋቋሙንም ገልፀዋል፡፡

በዓሉ በሚከበርበት ወቅትም የተለየ ነገር ሲያጋጥም በ8295 ወይም በ7614 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ መስጠት እንደሚቻል አመላክተዋል ፡፡

በተመሳሳይ የቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ ንግሥ ክብረ በዓል በሰላም እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ አስታውቋል።

የዞኑ ፖሊስ አዛዥና የበዓሉ አከባበር ግብረ ሃይል ሰብሳቢ ኮሚሽነር ናስር መሀመድ÷ የእንግዶችን ደህንነት ለመጠበቅ ከአጎራባች ክልሎች የጸጥታ ኃይሎች፣ ከመከላከያ ሠራዊትና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉ ማክበሪያ ሥፍራ የወንጀል ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ግለሰቦችን ለመቆጣጠርና ፈጣን ፍትህ ለመስጠትም ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያ፣ ዐቃቤ ሕግና ጊዜያዊ ፍርድ ቤት መቋቋሙንም ገልጸዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች በሕገ ወጥ ድርጊት የተሰማሩ ሰዎች ሲያጋጥሟቸው በስልክ ቁጥር 0256-662-090 ደውለው ጥቆማ በመስጠት ወንጀልን እንዲከላከሉ ኮሚሽነር ናስር አሳስበዋል።

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.