የነገዋ አዲስ አበባ ለማየትና ለመኖር የምታጓጓ ናት – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የነገዋ አዲስ አበባ ለማየትና ለመኖር የምታጓጓ ናት ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ፥ የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎ በአዲስ አበባ የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጉብኝቱ የኮሪደር፣ የአካባቢ ስነ ምህዳር ጥበቃ፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ ማህበራዊ ተቋማት፣ የፒያሳና ካዛንቺስ መልሶ ማልማትና የተነሺዎች ሁሉን አሟልተው የተገነቡ መንደሮችን መመልከታቸውን ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ በከተማዋ የተጠናቀቁና እየተፋጠኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ፈጠራና ፍጥነትን አስተሳስረው እየተከናወኑ መሆኑን ማየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ ለልማት ተነሺዎች የተገነቡ ቤቶች፣ የተቀናጁ የማህበራዊ ተቋማትና የመሰረተ ልማት ስራዎችም የነዋሪዎችን የቀድሞ ህይወት ከመለወጥ ባለፈ የፓርቲውን ሰው ተኮርነት በተጨባጭ ያረጋገጡ ተግባራት መሆናቸውንም ነው ያነሱት፡፡
የኮሪደር ልማት ከተሞችን የማብቃት ሥራ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከተሞቻችን ሲቆረቆሩ በታሪክ አጋጣሚ እንጂ በዕቅድ አልነበረም ፤ ይሄም ለኑሮ፣ ለቢዝነስና ለአገልግሎት ምቹ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል” ብለዋል።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የዘመናትን የከተማነት ፈተና የሚፈታ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ መኖሪያን፣ የሥራ ቦታን፣ ቢዝነስን፣ ቅርስን፣ ማኅበራዊ ትሥሥርን፣ እንቅስቃሴን፣ ጤናን፣ ጽዳትንና መዝናኛን በጥቅሉ የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻልን አማክሎ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የነገዋ አዲስ አበባ ለማየትና ለመኖር የምታጓጓ ናት ያሉት አቶ ተመስገን ፥ ተመሳሳይ ስራ ለጀመሩ የክልል ከተሞች ምሳሌና ሞዴልም ሆናለች ብለዋል፡፡