Fana: At a Speed of Life!

ከሕዳሴ ግድብ የመነጨው ሃይል በአግባቡ እየተከፋፈለ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የሆለታ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመነጨውን ሃይል በአግባቡ እያከፋፈለ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የጣቢያው ሃላፊ አቶ ጥላሁን አዘዘው እንደገለጹት÷የማከፋፈያ ጣቢያው እያንዳንዳቸው 750 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው ሰባት ትራንስፎርመሮች አሉት፡፡

ጣቢያው በአሁኑ ወቅት ከሕዳሴ ግድብ በአራት ተርባይን እየመነጨ ያለውን 1 ሺህ 500 ሜጋ ዋት ሃይል ከዴዴሳ ማከፋፈያ ጣቢያ ተቀብሎ ወደ ተለያዩ ማከፋፈያ ጣቢያዎች በማሰራጨት ከግሪዱ ጋር እንደሚያገናኝ ገልጸዋል፡፡

ጣቢያው ከደዴሳ በባለ 500 ኪሎ ቮልት አራት መስመሮች ሃይል ተቀብሎ በ400 ኪሎ ቮልት በጥምር መስመር ለሱሉልታ፣ ሰበታና ገላን ማከፋፈያ ጣቢያዎች ሃይል እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በ3 ባለ 33 ኪሎ ቮልትና በ6 ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ለተለያዩ አካባቢዎች ሃይል እያቀረበ የሚገኝ ሲሆን÷ በባለ 132 ኪሎ ቮልት መስመር ደግሞ ለሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሃይል እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀሪ ተርባይኖች ወደ ሥራ ሲገቡ የመነጨውን ሃይል በሙሉ ተቀብሎ በአግባቡ ለማከፋፈል ዝግጁ መሆኑን አቶ ጥላሁን አንስተዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ተርባይኖች 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም እንዳላቸው መጠቆሙንም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል መረጃ አመልክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.