በኮንትራት ፋርሚንግ ከለማው ሰሊጥ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2016/17 የምርት ዘመን በግብርና ምርት ውል (ኮንትራት ፋርሚንግ) ከለማው ሰሊጥ ከ1 ሚሊየን 369 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የግብርና ምርት ውል ዴስክ ኃላፊ ሱልጣን መሐመድ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች በ191 ሺህ 641 ሔክታር መሬት ላይ ሰሊጥ ለምቷል፡፡
አሁን ላይ የምርት መሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው÷ በአጠቃላይ በዘር ከተሸፈነው ውስጥ 1 ሚሊየን 369 ሺህ 48 ኩንታል የሰሊጥ ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡
ኮንትራት ፋርሚንግ ዘንድሮ ካለፉት ዓመታት አንጻር የተሻለ ዕድገት ማሳየቱን ጠቅሰው÷ በዘንድሮው የኮንትራት ፋርሚንግ ሥራ 44 ሺህ 337 ወንዶች እና 3 ሺህ 871 ሴት አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡
የኮንትራት ፋርሚንግ አርሶ አደሮች እና ገዥዎች የግብርና ምርት ገበያ ላይ ተመስርተው አስቀድመው ስምምነት የሚፈጥሩበት መንገድ ሲሆን÷ በስምምነቱ አብዛኛውን ጊዜ ለአርሶ አደሮች ሊከፈል የሚችልን ዋጋ፣ ለገዥዎች የሚቀርበው የምርት መጠን፣ ጥራት እና የምርቱ መቅረቢያ ጊዜውን ለይቶ የሚያስቀምጥ ነው።
በዮሐንስ ደርበው