የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ለተመልካች ክፍት ሆነ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ለተመልካች ክፍት እንዲሆኑ መወሰኑን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ እየተካሄዱ ሲሆን÷ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ ላይ ዘላቂ መፍትሔ እስከሚገኝ በዚህ ዙር የሚደረጉ ጨዋታዎች በዝግ እንዲደረጉ ትናንት ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተደረገ ውይይት ጨዋታዎች ለተመልካች ክፍት እንዲሆኑ መግባባት ላይ መደረሱን ነው የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመላከተው፡፡
ተጋጣሚ ክለቦች ደጋፊዎቻቸው ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ክለባቸውን እንዲደግፉ የማስተባበር ስራ እንዲሰሩ እና ክለቦችም ለስፖርታዊ ጨዋነት ቅድሚያ ሰጥተው ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡
ፌዴሬሽኑም የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት በሚፈፅሙ አካላት ላይ የማያዳግም ርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡