Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ የሴቶች እና ወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ የሴቶች እና የወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ እና የሚበረታታ እንደነበር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በምክክሩ ወቅት ሴቶች እና ወጣቶች በንቃት በመሳተፍ አጀንዳዎቻቸውን እንዳቀረቡ ተናግረዋል፡፡

በዚህም የወጣቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳደግ እና ሰላም ማስጠበቅን የተመለከቱና ተያያዥ አጀንዳዎች ከተሳታፊ ወጣቶች መቅረባቸውን አንስተዋል።

በተመሳሳይ ሴቶችም እኩል ተጠቃሚነትን፣ ሴቶችን ወደ አመራር ደረጃ ማሳደግ፣ ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች ላይ መሳተፍ እና በፖለቲካ ማብቃት የሚቻልባቸው መንገዶችን በተመለከተ ያላቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል ነው ያሉት፡፡

በተለይም ግጭቶች በሚከሰቱበት ጊዜ የሴቶች ተጎጂነት ከፍተኛ በመሆኑ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ዋና አጀንዳቸው መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ምዕራፍ 7 ሺህ 200 የማህበረሰብ ተወካዮች እና 2 ሺህ የሚደርሱ የባለድርሻ አካላት እና ተጽእኖ ፈጣሪዎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

አጠቃላይ ሂደቱ አካታች፣ የህዝቡ ባለቤትነት የታየበት፣ የህዝብ ውክልና የተረጋገጠበት እና መሰረታዊ ደረጃ ላይ የሚገኝ ዴሞክራሲያዊ ልምምድ የታየበት የተሳካ ሂደት እንደነበርም አስታውሰዋል።

በቀጣይ አጀንዳ የማሰባሰብ ምዕራፉ በአማራ ክልል ይጀመራል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ለዚህም ወደ ክልሉ በማቅናት መሰረታዊ የሎጂስቲክ ዝግጅት፣ ስልጠና እና ማህበረሰቡን በሥነ-ልቦና የማዘጋጀት ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡

በሄለን ታደሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.