የጦር መሳሪያ በሀይማኖት ተቋም ውስጥ ቀብሮ በመሸሸግ የተከሰሱ የአል-ሻባብ አባላት በ18 ዓመት እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጦር መሳሪያ በሀይማኖት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ ቀብሮ በመሸሸግ የተከሰሱ የአል-ሻባብ አባላት እስከ 18 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ ጅግጅጋ ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል።
በፍትህ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅ/ፅ/ቤት የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ 1ኛ አብሽር አህመድ፣ 2ኛ መሀመድ አሚን አብዱላሂ፣ 3ኛ መሀመድ ወይራ እና 4ኛ መሀመድ አብዲ በተባሉ የአሸባሪው አል-ሻባብ አባላት ላይ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን ጠቅሶ በታሳስ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
በዚህ ክስ ላይ እንዳመላከተው፤ ተከሳሾቹ የሽብር ቡድን አባል በመሆን የራሳቸውን የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ለማሳካት የሽብር ድርጊቶችን መፈጸም እንዴት እንዳለባቸው የአሸባሪነት ስልጠናዎችን ከወሰዱ በኋላ ሼህ መሀመድ ሀሰን በሚባል የሽብር ቡድኑ ክንፍ መሪ ትእዛዝ ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚጠቀሙባቸውን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ኢሜገልቤት ከሚባለው አካባቢ ከሚገኝ የሽብር ቡድኑ አባል በመቀበል ወደ ኤልከሬ ወረዳ በደው ቀበሌ ከ1ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት አጠገብ እና በአካባቢው በሚገኝ የሀይማኖት ተቋም ውስጥ 1ኛ ተከሳሽ 1 ብሬን እና 9 ክላሽንኮቭ፣ 2ኛ ተከሳሽ 7 ክላሽንኮቭ እና 3 ብሬን፣ 3ኛ ተከሳሽ 12 ክላሽንኮቭ እና 1 ብሬን እንዲሁም 4ኛ ተከሳሽ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን 4 ብሬን የጦር መሳሪያዎች በማምጣት ቀብረው ደብቀዋል።
መሳሪያዎቹ ከተደበቁበት ቦታ ላይ በፀጥታ አካላት በተደረገ ኦፕሬሽን መያዛቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዝርዝር ላይ ጠቅሷል።
በተለይም ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉት ተከሳሾቹ የጦር መሳሪያውን ቀብረው ካስቀመጡበት መገኘቱን ሲሰሙ ክላሽንኮቭ ታጥቀው ጫካ በመግባት የሽብር ቡድኑን ዓላማ ለማስፈጸም ተኩስ በመክፈት የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ አስፍሯል።
በዚህም መሰረት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የሽብር ወንጀል የቀረበባቸው ክስ ዝርዝር ደርሷቸው የወንጀል ድርጊቱን ክደው በመከራከራቸው ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃውን አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱ ማስረጃዎቹን መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ማስተባበል አለመቻላቸውን በማረጋገጥ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት በመያዝ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲሁም 4ኛ ተከሳሽ በ16 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ