በህዳሴ ግድብ ዓሳ የማምረት ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና በሌሎችም የሀገሪቷ አካባቢዎች ዓሳ የማምረት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እንዳሉት÷መንግስት ሀገሪቷ ጥራትና ብዛት ያላቸውን የዓሳ ምርቶች ማምረት የሚያስችላትን አቅም ለማሳደግ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎችን እንዲሁም አቅጣጫዎችን በማውጣት ወደ ተግባር ገብቶ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።
በመሆኑም በህዳሴ ግድብ እና በሌሎችም የሀገሪቷ አካባቢዎች ዓሳ የማምረት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ 9 ነጥብ 2 ሚሊየን የዓሳ ጫጩቶችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማሰራጨት አቅዶ በስፋት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በእስካሁኑ ሂደትም 4 ነጥብ 5 ሚሊየን የዓሳ ጫጩቶች ማሰራጨቱን ጠቅሰው፥በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በዓሳ ልማት ዙሪያ በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ በስፋት የማልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከሁለት ሳምንት በፊት 56 ቶን ዓሳ ማምረት ተችሏል ብለዋል።
በዘርፉ ልማት ለሚሰማሩ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸው የዘርፉን ልማት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ከመንግስት ጥረት ባለፈ የባለሃብቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር ጠይቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።