አደንዛዥ ዕጽ በመንግስት መኪና ሲያዘዋውር የነበረ ግለሰብ በ12 ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 21 ኩንታል ካናቢስ በመንግስት መኪና ሲያዘዋውር የነበረ ግለሰብ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ40 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ መቀጣቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።
ተከሳሽ ታምሩ ፍቅሬ የተባለው ግለሰብ ባለቤትነቱ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በሆነው ላንድ ክሩዘር ተሽከርካሪ 21 ኩንታል ካናቢስ በመጫን ከሻሸመኔ ዓለም ገና ወደ ሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በመውሰድ ላይ እያለ በደረሰ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉ ተነግሯል።
ፖሊስም ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ከነኤግዚቢቱ እጅ ከፍንጅ ይዞ የምርመራ ሂደት በሚገባ ካጣራ በኋላ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሽ ታምሩ ፍቅሬ ላይ 12 ዓመት ፅኑ እስራትና የ40ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ውሳኔ ማስተላለፉን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለመሰል የወንጀል ድርጊት እንዳይጋለጡ የተሽከርካሪዎቻቸው እንቅስቃሴ መቆጣጠር እንደሚገባቸው መልዕክት ተላልፏል፡፡