Fana: At a Speed of Life!

የህንጻ ግንባታዎች ርዕደ መሬትን መቋቋም በሚችሉበት ሁኔታ እንዲገነቡ በትኩረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የህንጻ ግንባታዎች ርዕደ መሬትን መቋቋም የሚችሉ ሆነው እንዲገነቡ በትኩረት እየሰራን ነው ሲል የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በባለስልጣኑ የኮንስትራክሽን ፕሮጄክት ቁጥጥርና ክትትል ዋና ስራ አስፈጻሚ በረከት ተዘራ ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ ህንጻዎች ሲገነቡ ለርዕደ መሬት እና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች በቀላሉ እንዳይጋለጡና ለችግሩ መንስኤ እንዳይሆኑ የቁጥጥርና የክትትል ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይም በቅርቡ በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌና አካባቢው የተከሰተውን ተደጋጋሚ ርዕደ መሬት መነሻ በማድረግ ከባለፈው በበለጠ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

በዚህም ባለስልጣኑ አደጋውን ለመከላከልና ለመቀነስ እንዲያስችለው ጥናት እያካሄደ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በባለስልጣኑ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ዲዛይን ቁጥጥር ዋና ስራ አስፈጻሚ ግሩም ፈይሳ በበኩላቸው የኮንስትራክሽን ግንባታዎች ሲገነቡ የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ካላገናዘቡ ለመሰል የተፈጥሮ አደጋዎች በቀላሉ ሊጋለጡና መንስኤ ሊሆንም እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ባለስልጣኑ አንድ ህንጻ ሲገነባ ምን ምን መስፈርቶችን ማሟላት አለበት የሚለውን በመለየት ፈቃድ እንደሚሰጥ አንስተዋል፡፡

በተለይ በቅረቡ ከተፈጠረው ተደጋጋሚ ክስተት በመነሳትም ባለስልጣኑ የቁጥጥርና የክትትል ስራውን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.