የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንደሚያስችል ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መሰረታዊ የኢኮኖሚ ለውጥ በማምጣት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንደሚያስችል የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበርና በጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና በይነ አፍሪካ ንግድ ጥናት ማዕከል በጋራ ያዘጋጁት የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሂዷል፡፡
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተፈሪ ጥያሩ÷ኢትዮጵያ በሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ የፖሊሲ ለውጥ ማድረጓ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን አንስተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫዎት መሆኑን ጠቅሰው፥በአጭር ጊዜ ችግር ዘላቂ ጥቅምን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማሻሻያው መሰረታዊ የኢኮኖሚ ለውጥ በማምጣት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንደሚያስችል ነው ያስረዱት፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደሃና(ፕ/ር) በበኩላቸው ÷የዶላር ዋጋ በገበያ እንዲተመን መወሰኑ በኢትዮጵያ ከታሰበው በላይ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲፈጠር ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በትይዩ መደበኛ ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ፣ የባንኮችን የመሸጫና የመግዣ ዋጋ በማቀራረብ አዎንታዊ ውጤት ተመዝግቧል ማለታቸውን የኢንስቲትዩቱ መረጃ አመላክቷል።
በጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና በይነ አፍሪካ ንግድ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ሰይፈ ታደለ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያውያን አብሮነትና በትብብር የመሥራት ባህል ለቀጣናዊ ትስስር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡