እዮቤል ፀጋዬ የፋና ላምሮት ምዕራፍ 18 የፍጻሜ ውድድር አሸናፊ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ላለፉት ሶስት ወራት በአስደናቂ ተወዳዳሪዎች ሲካሄድ የቆየው የፋና ላምሮት ምዕራፍ 18 ውድድር ዛሬ ተጠናቅቋል፡፡
ለፍጻሜው ማዕረግ ሀይሉ፣ እየሩሳሌም አሰፋ፣ ግሩም ነብዩ እና እዮቤል ፀጋዬ በሶስት ዙር የመረጧቸውን ሙዚቃዎች ከዛየን ባንድ ጋር አቅርበዋል፡፡
በውድድሩ እዮቤል ፀጋዬ አንደኛ በመውጣት ያሸነፈ ሲሆን÷ በዚህም የ400 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡
በተጨማሪም ግሩም ነብዩ ውድድሩን 2ኛ ሆኖ በማጠናቀቅ 300 ሺህ ብር የተሸለመ ሲሆን÷ ማዕረግ ሀይሉ ደግሞ 3ኛ በመውጣት የ200 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡
የፍጻሜ ውድድሩን 4ኛ ሆና ያጠናቀቀችው እየሩሳሌም አሰፋ የ100 ሺህ ብር ተሸላሚ መሆን ችላለች፡፡
የፋና ላምሮት የምዕራፍ 18 ውድድር መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ.ም በ16 ተወዳዳሪዎች የተጀመረ ሲሆን÷ተወዳዳሪዎቹም ለስምንት ሳምንታት በሁለት ምድብ ተከፍለው ሲወዳደሩ ቆይተዋል፡፡
በውድድሩ በየሳምንቱ አንድ ተወዳዳሪ የተሰናበተ ሲሆን÷ ከውድድሩ የተሰናበቱ ተወዳዳሪዎች ለእያንዳንዳቸው ከ5 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 35 ሺህ ብር ተሸልመዋል፡፡
ብርቱ ፉክክር በተደረገበትና በእየሳምንቱ በሁለት ዙሮች በተካሄደው በዚህ የፋና ላምሮት የምዕራፍ 18 ውድድር 10 ወንዶችና 6 ሴት ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለዚህ ውድድር በአጠቃላይ የ1 ሚሊየን ብር ሽልማት አዘጋጅቶ ተወዳዳሪዎችን መሸለሙን አስታውቋል፡፡
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አልአዛር ታደለ ÷ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በተሻለ አቅምና ዝግጅት የአድማጭ ተመልካቾችን ፍላጎት ለማርካት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ኮርፖሬሽኑ ለአድማጭ ተመልካች የሚያቀርባቸውን የሚዲያ ሥራዎች በቻናል 1 እና ቻናል 2 በመከፋፈል ዜናና ወቅታዊ ጉዳዮችን እንዲሁም የመዝናኛ እና ሌሎች ጉዳዮችን በላቀ ጥራት ይዞ ይመጣል ብለዋል፡፡
በመዝናኛው ዘርፍ በቀጣይም በስፋት እንሰራለን ያሉት አቶ አልአዛር÷ በዚሁ ዘርፍ ለሚሰሩ አካላት የአብረን እንስራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአመለወርቅ ደምሰው