Fana: At a Speed of Life!

የጤና ሚኒስቴርና ኢትዮ ቴሌኮም የጤና ዘርፉን በዲጂታል ለማዘመን ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና ሚኒስቴር እና ኢትዮ ቴሌኮም የጤና ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን ተስማምተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ሁለቱ ተቋማት በትብብር መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ዶ/ር መቅደስ ዳባ ዲጂታል ሄልዝ በጤና ሚኒስቴር ትኩረት ተሰጥቶት በጤና ፖሊሲ ውስጥ መካተቱን አስረድተው÷ ሚኒስቴሩ የቴሌ ሄልዝ አገልግሎት በፖሊሲ እንዲደገፍና በህጋዊ መንገድ እንዲመራ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

የቴሌኮምና የዲጂታል መሰረተ ልማትን በመጠቀም በማህበራዊ ሚዲያ የጤና ትምህርትና ትክክለኛ የጤና መረጃ ለማህበረሰቡ ማድረስ መቻሉን ገልጸው ÷ኢትዮ ቴሌኮም ለጤናው ዘርፍ እያቀረበ ስላለው የዲጂታል አገልግሎቶት አመስግነዋል፡፡

በጤና ተቋማት የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያመላከቱት፡፡

ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው÷ ከጤና ጋር መቀናጀት የሚፈልጉ በርካታ የዲጂታል አገልግሎቶች መኖራቸውን ከውይይቱ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም የጤና ተቋማትን አሰራር በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በማዘመን የአገልግሎት ጥራት መሻሻል ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የጤና ተቋማትን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የኔትወርክ እና የዲጂታል መሰረተልማት ማስፋፊያ የሚያደርግበትን የቴክኖሎጂ አማራጮች መለየቱንም አስረድተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.