Fana: At a Speed of Life!

ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከትናንት የተሻገሩ የፖለቲካ ስብራቶችን ለመጠገንና በሀገሪቷ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መንግስት ያደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ገለጹ።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ከለውጡ በኋላ ግጭት ይከሰትባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዱ እንደነበር አስታውሰው መንግስት ለሰላም ባደረገው ጥረት ሰላማዊ እልባት ማገኘቱን ገልጸዋል።

የግጭቱ ዋነኛ ምክንያት አካባቢው የማዕድንና የእርሻ እምቅ ሀብት የታደለ በመሆኑ እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገኛ በመሆኑ የልማት ጥረቱ እንዳይሳካ በሚሰሩ አካላት አነሳሽነት እንደነበርም አስታውሰዋል።

በመሆኑም በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቁርጠኝነት መስራቱን አንስተው፤ የክልሉ መንግሥትም የታጣቂዎችን ጥያቄ በመለየት በሰላም ለመፍታት ጥረት በማድረጉ መረጋጋት መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

በዚህም በክልሉ አስተማማኝ ሰላም በመፈጠሩ የልማት ስራዎችና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከፍተኛ መነቃቃት አሳይቷል ነው ያሉት።

የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ መንግስት ለዘላቂ ሰላም ያደረገው ጥረትና ያሳየው ቁርጠኝነት የሚጨበጥ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።

የሰላም ዋናው ምንጭ ልማት፣ የህዝብ ተጠቃሚነትና የስራ ዕድል መፍጠር መሆኑን አንስተው፤ ለልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራትና ቅሬታ የሚፈጥሩ ምክንያቶችን ማስወገድ የመንግሥትና የፓርቲው ዋነኛ ትኩረት መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ለአብነትም በትግራይ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ታጥቀው ይንቀሳቀሱ የነበሩ አካላትን ወደ ሰላማዊ አማራጭ በማምጣት ችግሮች እንዲፈቱ መንግስት ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል።

የሀገሪቱን የሰላምና የፖለቲካ ድባብ በዘላቂነት ለመቀየርም ከትናንት የተሻገሩ ፖለቲካዊ ስብራቶችን ለማቃናት የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በምክክርና በእርቅ ያለፈውን ችግር መሻገር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ የልዩነት አጀንዳ ያላቸው ሁሉ በአንድ ላይ በመምከር ችግሮች የሚፈቱበትና መግባባት የሚፈጥሩበት ሁሉንም አካታች ያደረገ ሀገራዊ የምክክር ሂደት መጀመሩን አንስተዋል።

ከውጭና ከውስጥ አንዳንድ አካላት ግጭትን እንደ ገቢ ማግኛ በመጠቀም በተለያዩ መንገዶች ግጭት አባባሽ ነገሮችን እያሰራጩ መሆኑን አንስተው፤ ዜጎች ይህንን በመረዳት ለሰላማቸው ዘብ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የጸጥታና ደህንነት ተቋማት የህግ ማስከበር ሚና የህዝብ ደህንነትን ማስጠበቅ ላይ በጠንካራ ቁመና እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም አፈንጋጮችን ወደ መስመር ለማስገባት ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ በኩል ከጎረቤት ሀገራ ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የትብብር እና የጋራ ልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ መንግሥት ህዝቡን ያሳተፈ ሥራ ላይ በመሆኑ ይህንን ሁሉም በመደገፍ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርገውን መንገድ መከተል ይገባል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.