Fana: At a Speed of Life!

ማንቼስተር ሲቲ ወደ አሸናፊነት ተመለሰ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለወራት በውጤት ቀውስ ውስጥ የቆየው ማንቼስተር ሲቲ ከ4 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በኋላ ሌስተር ሲቲን በማሸነፍ ሶስት ነጥብ አሳክቷል፡፡

በገና በዓል ሰሞን ከሜዳቸው ውጭ ሌስተር ሲቲን የገጠሙት ሲቲዝኖቹ በሳቪኒሆ ሞሬራ እና ኤርሊንግ ሃላንድ ጎሎች 2 ለ 0 አሸንፈዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ ጎል ያስቆረው ብራዚላዊው የማንቼስተር ሲቲ አጥቂ ሳቪንሆ ሞሬይራ ከ18 ሳምንታት የፕሪሚየር ሊጉ ቆይታ በኋላ የመጀመሪያ የሊግ ግቡን ማስቆጠር ችሏል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ በክለቡ ውጤት ማጣት ምክንያት ጫና ውስጥ የገቡት አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ እፎይታን ያገኙ ሲሆን ሲቲ ከነበረበት 7ኛ ደረጃ 31 ነጥቦችን በመያዝ በጊዜያዊነት 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

ማንቼስተር ሲቲ ባለፉት 4 ጨዋታዎች በማንቼስተር ዩናይትድ እና በአስቶንቪላ ሲሸነፍ ከኤቨርተን እና ክሪስታል ፓላስ ጋር ደግሞ ነጥብ መጋራቱ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በተደረጉ የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብሮች ኖቲንግሃም ፎረስት ኤቨርተንን 2 ለ 0 በማሸነፍ አርሰናልን እና ቼልሲን በነጠብ በመብለጥ በጊዜያዊነት ሁለተኛ ደረጃ መቀመጥ ችሏል፡፡

በሌሎች መርሃ ግብሮች፣ ፉልሃም ከቦርንማውዝ እንዲሁም ቶተንሃም ከዎልቭስ በተመሳሳይ 2 አቻ ሲለያዩ ክሪስታል ፓላስ ሳወዝሃምፕተንን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.