Fana: At a Speed of Life!

የሙዝ ምርትን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሙዝ ምርትን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመላክ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስታወቀ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ፤ ክልሉ ለሙዝ ተክል ምቹ ስነ-ምህዳር ያለው በመሆኑ በአሁኑ ወቅት 113 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ መሆኑን ገልፀዋል።

በአምስት ወራት 15 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የሙዝ ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰው፤ በበጀት ዓመቱ 35 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

በክልሉ የሚመረተው ሙዝ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደሚሰራጭ የተናገሩት ሃላፊው፤ ከሀገር ውጪ ወደ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ እንደሚላክ ጠቁመዋል።

ከእነዚህ ሀገራት በተጨማሪ ምርቱን ወደ መካከለኛው ምስራቅም ሀገራት ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

የሀገራቱ ገበያ የሚፈልገውን ጥራት፣ መጠንና ሌሎች መስፈርቶች ለማሟላት የሚያስችል የሙዝ ዝርያ ችግኝ ከውጭ የማስገባትና የማባዛት ስራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ኃይለማርያም ጠቁመዋል።

በሙዝ ምርት ልማት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሞዴል አርሶአደር በሄክታር ከ400 እስከ 450 ኩንታል በኢንቨስትመንት ማሳ እስከ 500 ኩንታል ምርት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

የስራ እድል በመፍጠርና ገቢ በማመንጨት ረገድ የጎላ አስተዋፅዖው ያለው የሙዝ ተክል በክልሉ በ12 ቱም ዞኖች እየለማ ሲሆን÷ ጋሞ፣ ወላይታ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ከፍተኛ ሽፋኑን እንደሚይዙ ተነግሯል።

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.