Fana: At a Speed of Life!

ከ250 በላይ የአየር ሁኔታ መከታተያዎችን በመትከል የመረጃ ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 250 ሰው አልባ የአየር ሁኔታ መከታተያ ጣቢያዎች በመትከል የመረጃ ተደራሽነቱን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

300 በሚጠጉ ሰው አልባ እና ከ1 ሺህ 300 በሚልቁ በሰው መረጃ በሚመዘግቡ የተለያየ ደረጃ ባላቸው የአየር ሁኔታ መከታተያ ጣቢያዎች በመላ ሀገሪቱ መረጃ እየተሰበሰበ መሆኑን በኢንስቲትዩቱ የመሰረታዊ ሚቲዎሮሎጂ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክንፈ ኃ/ማርያም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም 17 በሚደርሱ በአውሮፕላን ጣቢዎች የተቋቋሙ ሰው አልባ፣ ሁለት የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳሮች እና ሦስት የአየር ብክለት መከታተያ ጣቢያዎችን በመጠቀም ኢንስቲትዩቱ መረጃ በመሰብሰብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይም ከመንግሥት በጀት እና የልማት አጋሮች በተገኘ ድጋፍ ሁለት ተጨማሪ የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር፣ 10 ተንቀሳቃሽ የአየር ብክለት መከታተያ ጣቢያ እንዲሁም እስከ 250 የሚደርሱ ሰው አልባ የአየር ሁኔታ መከታተያ ጣቢያዎች በመትከል የመረጃ ክፍተትን ለማጥበብ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

እነዚህ ሰው አልባ ጣቢያዎች አብዛኛዎቹ የሚቋቋሙት በአርብቶ አደሩ አካባቢ እና የጣቢያ ሽፋን ዝቅተኛ በሆነባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች መሆናቸውን አስታውቀው÷ ሲጠናቀቁ የመረጃ ተደራሽነቱን ያሳድጉታል ብለዋል፡፡

ኢንስቲትዩት የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ ትንበያዎች ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እንደሚያደርግ የገለጹት ደግሞ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ትንበያዎቹ የሚዘጋጁት ከመሬት እስከ ከባቢ አየር ውስጥ በሚሰበሰቡት መረጃዎች ላይ አሀዛዊ ትንታኔዎችን በማካሄድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የሚሰጠው የአጭር ጊዜ ትንበያ 82 ከመቶ እንዲሁም የረዥም ወቅት ትንበያ ትክክለኛነት 78 በመቶ መሆኑን የጥናት ውጤት ማመላከቱን ጠቅሰዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.