የጎግል ክሮም መጠለፍ ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተጠቃሚዎችን ለዳታ ስርቆት ማጋለጡ ተነገረ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጎግል ክሮም መጠለፍ ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተጠቃሚዎችን ለዳታ ስርቆት እንዳጋለጠ ተነግሯል፡፡
ጥቃቱ ያነጣጠረው በክሮም ድር ማሰሻ ቅጥያዎች ላይ ሲሆን ጥቃቱ የተፈጸመበት መንገድ በአስጋሪ ዘመቻ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም ኩኪዎችን እና የተጠቃሚ መዳረሻ ለመስረቅ የማጭበርበሪያ ኮድ ወደ ህጋዊ ቅጥያዎች ለማስገባት የመዳረሻ ፈቃዶቻቸውን መጠቀሙ ተገልጿል።
በጥቃት መጋለጡ የታወቀው የመጀመሪያው ኩባንያ “ሳይበርሃቨን” የተሰኘው የሳይበር ደህንነት ድርጅት መሆኑ ተመላክቷል።
በፈረንጆቹ ታሕሣሥ 27፣ ሳይበርሃቨን ይፋ እንዳረገው ጥቃት የሰነዘረው አካል የአሳሹን ቅጥያ እንደጣሰ በዚህም ከውጭ ያለ አካል በሳይበርሃቨን ሰርቨር የተመዘገበ ዶሜይን ላይ ትእዛዝ እንዲሰጥ እና እንዲቆጣጠር፤ ፋይሎችን እንዲያወርድ እና የተጠቃሚዎችን መረጃ እንዲያወጣ የሚያስችል የማጭበርበሪያ ኮድ መላኩን ገልጿል፡፡
ሳይበርሃቨን ድርጅት ጥቃት እንደደረሰበት ይፋ ካደረገ በኋለ ሌሎች የክሮም ማሰሻ ቅጥያዎች በጥቃቱ እንደተጋለጡ ተጠርጥሯል።
ከእነዚህም ውስጥ ኤአይ አሲስታንት-ቻት ጂፒቲ፣ ባርድ ኤአይ ቻት ኤክስቴንሽን፣ ሰርች ኮፓይለት ቪዲዮ ዳውንሎደር እና ሌሎችም እንደሚገኙበት ከኢትዮጵያ መረጃ ደህንነት አስተዳደር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡