አየር መንገዱ ወደ ላሊበላ እና ጎንደር ከተሞች ከመደበኛው ተጨማሪ በረራዎችን አዘጋጀ
አዲስ አበባ፣ ታሕሳስ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጪዎቹ ሳምንታት የሚከበሩትን የገና እና የጥምቀት በዓላት ለማክበር ወደ ላሊበላ እና ጎንደር ከተማ ለሚጓዙ ደንበኞቹ ከሚያደርገው መደበኛ ዕለታዊ በረራ ተጨማሪ በረራዎችን ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
በዓላቱ እንደወትሮው ሁሉ በድምቀት እንዲከበሩ ሀገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ነው አየር መንገዱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያስታወቀው፡፡
በዓላቱ ከሐይማኖታዊ ይዘታቸው ባለፈ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ጎብኚዎች በስፋት የሚታደሙባቸው ስለሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአየር በረራን በበቂ ሁኔታ በመመደብ የተለመደውን የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡
እነዚህ ተጨማሪ በረራዎች ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ያለምንም መንገደኛ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ የዋጋ ማስተካከያ በተጨማሪ በረራዎቹ ላይ ብቻ እንደሚደረግም ነው የተገለጸው፡፡
የሚደረገው የዋጋ ማስተካከያ ወደ ከተሞቹ የሚደረጉትን መደበኛ በረራዎች የማይመለከት መሆኑንም አየር መንገዱ አስገንዝቧል፡፡