Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው የበዓል ግብይትን ለመከታተልና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የተቋቋመ ግብረ ኃይል ወደ ሥራ መግባቱንም አስታውቋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ አስር ኢብራሂም መጪውን የገና በዓል ህብረተሰቡ በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲያከብር የንግዱ ማህበረሰብ በሃላፊነት ስሜት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የግብርናም ሆነ የፋብሪካ ውጤቶች በተሻለ ደረጃ ለገበያ በመቅረብ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው የተቋቋመው ግብረ-ኃይል ከከተማ አስተዳደርና ወረዳዎች ጋር በመተባበር ገበያው እንዲረጋጋና ህብረተሰቡ በዓሉን በሰላም እንዲያሳልፍ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ብለዋል፡፡

የንግዱ ማሕበረሰብ በበዓላት ሰሞን ያለአግባብ ለመበልጸግ በመሞከር ከሚያደርገው ህገወጥ ድርጊት እንዲቆጠብም ኃላፊው ማሳሰባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ቢሮው ህግን በመተላለፍ ያለአግባብ ለመበልጸግ ሲሰሩ በሚገኙ አካላት ላይ ተገቢውን አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም ተመላክቷል፡፡

ህብረተሰቡ ያለአግባብ ዋጋ የሚጨምሩና ምርት የሚደብቁ አካላትን በመጠቆም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል፡፡

ህብረተሰቡ ህገ ወጥ ድርጊት ሲመለከት በ0930300655፣ 0917175792፣ 0928597221፣ 0913065072፣ 0917709593 እና 0917180003 የስልክ ቁጥሮች በመጠቀም ጥቆማ እንዲሰጥም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.