አምስት ሚሊየን ኮደሮች ኢንሼቲቭ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት እንደሚያስችል ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አምስት ሚሊየን ኮደሮች ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዲጂታል ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለመፍጠር እንደሚያስችል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለምፀሐይ ጳውሎስ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት 5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ የመጀመሪያ ዙር ማጠቃለያ መርኃ ግብር ተካሂዷል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት ሚኒስትሯ መንግሥት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን ዕውን ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለስኬቱ በዘርፉ የሰው ኃይልን ለማፍራት ከተተገበሩ መርኃ ግብሮች መካከል የአምስት ሚሊየን ኮደሮች ኢንሼቲቭን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኢንሼቲቩ ኢትዮጵያን በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ የሰው ኃይል ማፍራት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቻና (ዶ/ር) በ5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስጀመሩት የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ሥልጠና የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዘውን ጥረት ለማሳካት እየተሰራ እንደሚገኝ የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።