ዓለም አቀፍ የመስኖና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምርታማነት ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሳስ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የመስኖና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምርታማነት ጉባኤ 2025 በአዲስ አበባ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ።
ከየካቲት 5 እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደው ጉባኤ የዓለምና አህጉር አቀፍ መሪዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑም ታውቋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)÷ የኮንፍረንሱ ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ዝግጅት ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር በጉባኤው የኢትዮጵያ የመስኖ ልማት ልምድና ተሞክሮ የሚቀርብ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አሀጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በተሳካ መልኩ በማስተናገድ ተመራጭ መሆኗን አንስተው የአሁኑ ጉባኤም ስኬታማ እንዲሆን ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡