በግብዓት አቅርቦትና በሜካናይዜሽን እርሻ የተጀመሩ ስራዎች ለውጥ እያመጡ ነው-አቶ ጌታቸው ረዳ
አዲስ አበባ፣ ታሕሳስ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ክልልን የግብርና አሰራር ለማዘመን በግብዓት አቅርቦትና በሜካናይዜሽን እርሻ የተጀመሩ ስራዎች ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ።
”ትኩረት ለትግራይ ክልል ግብርና ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም በመቐለ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በሲምፖዚየሙ ላይ የተገኙት አቶ ጌታቸው ረዳ÷ የክልሉን የግብርና እና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመለወጥ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
”የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር ግብርናን ትራንስፎርም ለማድረግና የተጎዳው የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲንሰራራና የተሻለ ለውጥ እንዲያመጣ ሁሉንም ዓይነት ርብርብ እናደርጋለን” ብለዋል።
ግብርና የክልሉ ኢኮኖሚ ምሰሶ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፣ በግብዓት አቅርቦትና በሜካናይዜሽን ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ለውጥ እያመጡ መሆኑን አመልክተዋል።
በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢያሱ አብረሃ በበኩላቸው÷ያለውን አቅም በማቀናጀት የግብርና ምርትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃን ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሲምፖዚየሙም በዘርፉ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ዙሪያ የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ ለግብርናው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልፀዋል።