Fana: At a Speed of Life!

ከመኸር እርሻ 320 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2016/17 ምርት ዘመን የመኸር ወቅት እርሻ እስካሁን 320 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ ከበደ ላቀው እንዳሉት፤ በምርት ዘመኑ የመኸር ወቅት በኩታ-ገጠም የለማውን 11 ሚሊየን ሄክታር ጨምሮ 20 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል።

ከዚህም እስካሁን በ16 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ያለው የሰብል ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰው፤ እስካሁን 320 ሚሊየን ኩንታል ምርት ወደ ጎተራ መግባቱን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።

በአርሶ አደሩ ጉልበት ከሚሰበሰበው ምርት በተጨማሪ በሜካናይዝድ ዘዴ ምርት የመሰብሰብ ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ ቀሪውን ምርት ለመሰብሰብ በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ደጋ እና ወይናደጋ የአየር ፀባይ ባላቸው አካባቢዎች የሰብል ምርት አሰባሰቡ መቀጠሉንም አንስተዋል።

ጊዜውን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሰው ምርት ላይ ጉዳት እንዳያስከትል በሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ መሰረት ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረው፤ በምርት አሰባሰብ ወቅት ብክነት እንዳይከሰት ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.