የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ታሕሳስ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ያስችላል ያለውን የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ በአንድ ተቃውሞ፣ በዘጠኝ ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬው እለት 13ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡርቃ (ዶ/ር)÷ የጤና አገልግሎት እና ቁጥጥር አዋጅን አስመልክቶ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
አዋጁ የጤና ተቋማት፣ የምግብና መጠጥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ጤና ነክ ተቋማት አግባብነት ባላቸው ህጎች ውስጥ ስለቆሻሻ አያያዝ በተደነገገው መንገድ ቆሻሻን የመያዝ እና የማስወገድ ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡
የትኛውም ተቋም ይሁን ግለሰብ ቆሻሻን በአግባቡ መያዝና ማስወገድ እንዳለበትና ወደፊትም የበታች ህግ ሊወጣለት እንደሚገባ ለመጠቆም ሲባል አዋጁ መዘጋጀቱም ተጠቁሟል፡፡
በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችንና ተቋማትን ተጠያቂ የሚያደርግ ድንጋጌ ማስቀመጥ አስፈላጊ በመሆኑ በአዋጁ ከተደነገገው ውጭ ያለፈቃድ የሰውነት አካልን ወይም አካል ክፍልን የወሰደ ሰው ከ5 ዓመት በማያንስ እና ከ10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣም በአዋጁ መካተቱ ተጠቅሷል፡፡
በየሻምበል ምሕረት