የኢራን ፓርላማ ልዑክ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎበኘ
አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢራን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ መሐመድ ጋሊባፍ የተመራ ልዑካን ቡድን የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝቷል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና ላይ መሆኗን መረዳታቸውንና በጉብኝቱም መደሰታቸውን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ጥንታዊና ታሪካዊ ሀገር ናት ያሉት የልዑካን ቡድኑ አባላት ÷ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ካደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵያውያንን አንድነት፣ አይበገሬነትና ጀግንነት መረዳታቸውን አብራርተዋል።
እንዲሁም የኢትዮጵያን ታሪክ በመረዳታቸው እና ታሪካዊ ቁሳቁሶችን በማየታቸው መደሰታቸውንም የልዑካን ቡድኑ አባላት ተናግረዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የኢትዮ-ምዕራብ እስያ የወዳጅነት ቡድን ሰብሳቢ መሐመድ አሊ አል አሩሲ÷ የኢትዮጵያና ኢራን ፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲ እንዲጠናከር እንደፓርላማ እንሰራለን ብለዋል።
ጉብኝቱም የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ለማስተዋወቅና ለሀገሪቱ ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም መገለጹን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡