በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ180 ሺህ ኩንታል በላይ በርበሬ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ2016/17 የምርት ዘመን እስካሁን ከ180 ሺህ ኩንታል በላይ የበርበሬ ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
በቢሮው የቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ሃላፊ አቶ ተፈራ ዘርፉ እንዳሉት÷ በበጀት ዓመቱ የበርበሬ ምርትን በስፋት አምርቶ ለገበያ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ተሰርቷል፡፡
ክልሉ ከፍተኛ የበርበሬ አምራች ከሆኑ አካባቢዎች ውስጥ በቀዳሚነት እንደሚጠቀስ ገልጸው÷ በዚህም በምርት ዘመኑ 344 ሺህ ኩንታል በርበሬ ለማምረት መታቀዱን አንተዋል፡፡
ለምርት ውጤታማነትም በሽታን መቋቋም የሚችሉ የተሻሻሉ የበርበሬ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ድረስም ከ180 ሺህ ኩንታል በላይ የበርበሬ ምርት ተሰብስቦ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ገበያዎች እየቀረበ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የበርበሬ ገበያ ትስስሩን በመላ ሀገሪቱ ይበልጥ ለማሳለጥና ጥራቱን የጠበቀ በርበሬ ለገበያ ለማቅረብ ከባለሙያ እገዛ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
የበርበሬ ምርትን ውሃ አርከፍክፎ ለገበያ ማውጣት በስፋት የሚስተዋል ችግር መሆኑን ጠቁመው÷ ነጋዴዎች የበርበሬውን ጥራት ከሚጎዱ መሰል ድርጊት እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡
በአንጻሩ የበርበሬ ምርትን እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ተፈላጊነቱን መጨመር እንደሚቻል ሃላፊው አስገንዝበዋል፡፡
የበርበሬ ምርት በክልሉ በሚገኙ የስልጤ፣ ጉራጌ፣ ምስራቅ ጉራጌ፣ ከንባታ፣ ሃድያ፣ ሃላባና የም ዞኖች እንዲሁም የማረቆ ልዩ ወረዳን ጨምሮ በክልሉ በስፋት እንደሚመረት አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ