ክልሎች የከተራና ጥምቀት በዓልን ለማክበር መዘጋጀታቸውን አስታወቁ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋምቤላ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የከተራና ጥምቀት በዓል ለማክበር አስፈላጊ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
በጋምቤላ ክልል የከተራና ጥምቀት በዓል ያለምንም የፀጥታ ስጋት እንዲከበሩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ኡጉላ ኡጁሉ ገልጸዋል።
በዓሉ ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ከሁሉም የፀጥታ አካላት የተውጣጣ ግብረሃይል መቋቋሙን ገልጸው፤ በበዓሉ ወቅት ችግሮች ቢከሰቱ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ፈጣን ችሎት መቋቋሙንም አመልክተዋል።
በሲዳማ ክልል የጥምቀት በዓል ከወንጀል ነጻ ሆኖ እንዲከበር የተቀናጀ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ የጥምቀት በዓል ጸጥታን ለማስጠበቅ እቅድ መዘጋጀቱን ገልጸው፤ በዓሉ በክልሉ ሐዋሳ ከተማን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች በድምቀት የሚከበር መሆኑን አንስተዋል።
የጸጥታ አካላት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የከተራና የጥምቀት በዓል ከወንጀል ነፃ ሆኖ እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሰብስቤ ሻዎኖ ገልጸዋል።
ሊከሰቱ የሚችሉ የተለያዩ የስርቆት ወንጀሎችን ቀድሞ ለመከላከል በባህረ ጥምቀቱ እና አቅራቢያ በሆኑ አካባቢዎች ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያዎች መቋቋማቸውንም ጠቁመዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አብርሀም ቲርካሶ በበኩላቸው፤ በዓሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር ከዞን ጀምሮ ባሉ መዋቅሮች የፀጥታ አካላትና ማህበረሰቡን በማሳተፍ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የከተራና የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ወቅት ምዕመናን ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የጥምቀት በዓል ህብረ ብሔራዊ አንድነትንና የእርስ በርስ ትስስርን በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸው።
በዓሉ የቱሪስቶች መስህብና መዳረሻ በመሆን ለሀገርም ሆነ ለድሬዳዋ የምጣኔ ሃብት ዕድገት መሠረታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።