Fana: At a Speed of Life!

ለሰላም አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ ታጣቂዎች በሀገረ መንግስት ግንባታ እንዲሳተፉ ድጋፍ ይደረጋል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሰላም አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ የታጠቁ ቡድኖች በሀገረ መንግስት ግንባታ ሥራዎች በንቃት እንዲሳተፉና የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ፤ የሰላም አማራጮችን በመምረጥ ለሚገቡ ሁሉ አሁንም የሰላም በሩ ክፍት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

መንግስት ሁሉንም የሚያሳትፍና የሚያግባባ፣ አብሮነትን በትብብር የሚያጎለብት፣ ብዝኃነትንና አንድነትን የሚያሳልጥ በብሔራዊ ትርክት ላይ የተመሰረተ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ጥረት እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ይህ ነፃ ገለልተኛና ብቃት ያለው ተቋማትን በመገንባት ለትውልድ ተሻጋሪ እና ጠንካራ ሀገረ መንግስትን ለመገንባት የሚያስችል ሁኔታን እየፈጠረ መሆኑን ገልፀው፤ በዚህም አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ያለፉ ቁርሾ እና ስብራቶችን የሚጠግን፣ የትብብር ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ፣ ባህልን የሚያጎለብት የሽግግር ፍትህ ለመተግበር የሚያስችል የፖለቲካ መደላድል እየተፈጠረ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በዚህም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በክልሎች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመምከር አጀንዳ ማሰባሰብ መቻሉን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በአማራና ትግራይ ክልሎች ተመሳሳይ ሥራ ለመስራት ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠረ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ለሰላም አዎንታዊ ምላሽ የሰጡና የታጠቁ ቡድኖች ሀገሪቱ የሰላምና ብልፅግና ጉዞ ሂደት ውስጥ ሊጫወቱ የሚችሉትን ወሳኝ ሚና መንግስት ይገነዘባል ያሉት ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፤ ለዚህም መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.